የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በአስተዳደሩ የይግባኝ ሰሚ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማ አካሄደ።

በግምገማው እንደተመለከተው፣ የሁለቱ ፍርድ ቤቶች የፋይል አያያዝን ወደ ዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓት መለወጡና የድምፅ እና የምስል ቀረጻ ሥርዓትን በችሎት መጠቀም መጀመሩ፣ የፍትህ አሰጣጡን ይበልጥ ቀልጣፋና ግልጽ እንዳደረገው ተገልጿል።

በተጨማሪም በባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት፣ በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች የመጀመሪያ ደረጃ እና በአራቱም ክላስተር ደግሞ የይግባኝ ሰሚ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የተከናወኑ ተግባራት በሪፖርቱ በስኬት ተነስተዋል። ይህ እርምጃ ማህበረሰቡ ሳይንገላታ በአከባቢው በባህሉና በወጉ መሠረት የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስቻለ መሆኑ ተመላክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አህመድ አብደላ፣ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገለልተኝነትን፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን ቀጣይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። አክለውም፣ ውስብስብ የሆኑ የፍርድ አሰጣጥ ሂደቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የዜጎችን የፍትህ ተጠቃሚነትና ግልጽነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመጨረሻም፣ ፍርድ ቤቶች የተጀመረውን ባህላዊ የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓትን የበለጠ ውጤታማ ለማደረግ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ተጠናክሮ መቀጥል እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሳስበዋል

Leave a Comment